Friday, October 18, 2019

ከኢህአዴግ ምክር ቤት ፅ/ቤት የተሰጠ መግለጫ

ከኢህአዴግ ምክር ቤት ፅ/ቤት የተሰጠ መግለጫ
ኢህአዴግን ከግንባርነት ወደ አንድ ህብረ ብሄራዊ ውህድ ፓርቲ የማሸጋገር ጉዳይ በ1996 ዓ.ም ከተካሄደው 5ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ጀምሮ በተከታታይ በተካሄዱት የድርጅቱ ጉባዔዎችና የተለያዩ ድርጅታዊ መድረኮች ሲነሳ የቆየ ጥያቄ እንደሆነ ይታወቃል። በሁሉም የኢህአዴግ መድረኮች በውህደቱ አስፈላጊነት ላይ ስምምነት እየተያዘበት የሄደ ሲሆን በየጉባዔዎቹ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ውህደቱን በጥናት ላይ ተመስርቶ ለመፈፀም የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ቆይተዋል። ይልቁንም በቅርብ ጊዜያት በተካሄዱ ጉባዔዎች ይነሳ የነበረው ቁልፍ ችግር በአፈፃፀሙ ላይ የታየው ከፍተኛ መጓተት ነበር። በተለይ ባለፈው አመት በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው 11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ የጥናት ስራው በቶሎ ተጠናቆ የኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ውህደት ፈጥረው አንድ ጠንካራ ሀገራዊ ፓርቲ እንዲፈጠር ውሳኔ ተላልፏል። በሂደቱ የአጋር ድርጅቶችም ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ ተቀምጧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የውህደቱ አቀንቃኝ ሆኖ ውህደቱን ሲመራ የነበረው ህወሃት በአሁኑ ወቅት ውህደቱን በተመለከተ አሉታዊ ገፅታ ያላቸው ተደጋጋሚ መግለጫዎችን በማውጣት ላይ ይገኛል። ምንም እንኳን ጉዳዩ በሂደት ላይ ያለና ያልተቋጨ በመሆኑ በዚህ ወቅት መግለጫ መስጠትም ሆነ በሚወጡ የተሳሳቱ መግለጫዎች ላይ መልስ መስጠት አስፈላጊ አይደለም በሚል እምነት ጉዳዩን በዝምታ ለማለፍ የተሞከረ ቢሆንም የተሳሳቱ መረጃዎች ተደጋግመው ሲወጡ ችላ ማለት ደግሞ ህዝቡ ውስጥ መደናገርን ሊፈጥር የሚችል መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ለህዝቡ ጠቅለል ያለ መረጃ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
ህወሃት እንደ ድርጅትም ሆነ በአንዳንድ አመራሮቹ በተደጋጋሚ የሚሰጣቸው መግለጫዎች በሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች ስህተት ሆነው እናገኛቸዋለን። የመጀመሪያው ስህተት ከድርጅት አሰራርና ዲስፒሊን ጋር የተያያዘ ነው። በድርጅቱ አሰራርና ህገ ደንብ መሰረት የግንባሩ አባል ድርጅቶች በማንኛውም አጀንዳ ላይ ውይይትና ክርክር ካደረጉ በኋላ የመሰላቸውን አቋም መያዝና በአቋማቸውም ላይ ተመስርተው ክርክራቸውን መቀጠል የተለመደ ነው።
በ2011 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው 11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ህወሃትን ጨምሮ ሌሎች አጋርና አባል ድርጅቶች ጥናቱ በአፋጣኝ ተጠናቆ ወደ ተግባር እንዲገባ ያለልዩነት ወስነዋል። በውሳኔው መሰረት ተጠንቶ በቀረበው ሃሳብ ላይ ደግሞ ሁሉም ድርጅቶች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፤ ጥናቱ እንዲዳብርም የበኩላቸውን ተሳትፎ አድርገዋል። በአሁኑ ሰዓት እየተካሄዱ ያሉ ውይይቶችም ከውሳኔ በፊት ጥናቱን የሚያዳብሩ ሃሳቦችን የማሰባሰብ ሲሆኑ በዚህ ደረጃ በተካሄዱ የአመራር ውይይቶች ህወሃትም ሆነ ሌሎች አባልና አጋር ድርጅቶች ተሳትፈዋል፤ አስተያየታቸውንም ሰጥተዋል። የተሰጡት አስተያየቶች ጥናቱን ለማዳበር ወይም ያልታዩ ጉዳዮች በአግባቡ እንዲዳሰሱ ለማድረግ እንጂ የውሳኔ ወይም የአቋም ጉዳይ ሆነው የሚቀርቡ አልነበሩም። በመሆኑም ይህ አጀንዳ ገና በጥናት ውጤቱ ላይ ውሳኔ ያገኘበት ደረጃ ላይ አልደረሰም። የመጨረሻ የውህደት ውሳኔም አሰራሩን ጠብቆ ወደፊት የሚታይ ይሆናል። ጉዳዩ በዚህ ደረጃ ባለበትና የመጨረሻ ውሳኔ ተሰጥቶ የሁሉም ድርጅቶች አቋም ባልተገለፀበት ሁኔታ ህወሃት አስቀድሞ ለብቻው በተደጋጋሚ መግለጫ መስጠቱ የድርጅት አሰራርና ዲሲፒሊንን የጣሰ እንዲሁም ወቅቱን ያልጠበቀ በመሆኑ መታረም ያለበት ነው።
የመግለጫው ሁለተኛው ስህተት ደግሞ ይዘቱ ነው። ህወሃት በተለያዩ መግለጫዎቹ ደጋግሞ የሚያነሳው ውህደቱ አሃዳዊ መንግስት ለመመስረት የታቀደ አስመስሎ ማቅረብ ነው። ፓርቲው ወደ አንድ ወጥ ፓርቲ በሚቀየርበት ወቅት ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብታቸው እንደሚገፈፍና ፌዴራላዊ ስርዓቱ ፈርሶ አሃዳዊ ስርዓት እንደሚመስረት አድርጎ የሚያቀርበው ሃሳብ ለማደናገሪያ ካልሆነ በስተቀር ለመከራከሪያ የሚሆን ተጨባጭ ነገር የለውም። በመሰረቱ የአንድ ሀገር የመንግስት አወቃቀር የሚወሰነው በሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎና በኢትዮጵያ ህዝብ ውሳኔ እንጂ በአንድ ፓርቲ ፍላጎት ብቻ ሊሆን አይገባውም። ስለዚህ የኢህአዴግ ውህደት ለብቻው የአገሪቱን የፌዴራል ስርዓት የሚያፈርስ አድርጎ ማቅረብ ውሃ የሚቋጥር መከራከሪያ አይደለም።
ኢህአዴግ ወደ ውህደት መጥቶ ጠንካራ ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ ቢሆን ሀቀኛ ፌዴራሊዝምን እውን በማድረግ እኩልነትና ፍትህ የነገሰባት፣ አንድነቷ የተጠናከረና የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ይታገላል እንጂ የብሄር ብሄረሰቦችንንና ህዝቦችን መብት የሚሸራርፍበት ምንም ምክንያት የለውም።
ጥናቱን ያስጠኑት ህወሃትን ጨምሮ ሁሉም የኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ሲሆኑ የውህደቱ መነሻ ሃሳብም ሆነ የጥናቱ ውጤት ከአሃዳዊ ስርዓት ጋር ፈፅሞ ግንኙነት እንደሌለው ሁሉም ድርጅቶች በግልፅ የሚያውቁት ጉዳይ ነው። ስለሆነም ጉዳዩን ሁሉም የግንባሩ አባልና እህት ድርጅቶች በግልፅ የሚያውቁትና ወደፊት ውህደቱ ቢፈፀም ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች በግልፅ የሚገነዘቡት ሆኖ ሳለ እንዲህ አይነት የተዛባ መረጃ መስጠት መሰረታዊ ስህተት ነው።
ሌላኛው የመግለጫው ችግር የውህደት አጀንዳውን አሁን ያለው የለውጥ አመራር በድንገት ያመጣው በሚያስመስል መልኩ ማቅረቡ ነው። ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው የውህደት አጀንዳው መነሳት የጀመረው ረዘም ካሉ አመታት በፊት እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ደግሞ በድርጅቱ ጉባዔዎች፣ ምክር ቤትና ስራ አስፈፃሚ ስብሰባዎች ቃለ ጉባዔዎች ላይ ተመዝግቦ የሚገኝ እውነታ ነው። ሌላው ቀርቶ በአሁኑ ሰዓት ተጠናቆ ለውይይት የቀረበው ጥናት የተጀመረው አሁን ያለው አመራር ወደ ሃላፊነት ከመምጣቱ በፊት እንደሆነ በግልፅ የሚታወቅ ነው። አሁን ያለው የለውጥ አመራር የሰራው ነገር ቢኖር ለረጅም አመታት በልዩ ልዩ ምክንያት ሲጓተት የቆየውን ጥናት እንዲጠናቀቅ በማድረግ ለውሳኔ የሚቀርብበት ደረጃ ላይ ማድረስ ብቻ ነው። ስለሆነም በድርጅቱ ስም በሚወጡ መግለጫዎችም ሆኑ አንዳንድ አመራሮች በሚሰጧቸው ማብራሪያዎች የውህደቱን ሃሳብ አዲሱ የለውጥ አመራር በስልጣን ላይ ለመቆየት ሲል እንዳመጣው አስመስሎ ለህዝብ ማቅረብ የተሳሳተ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም።
በአጠቃላይ ኢሕአዴግን ወደ አንድ ህብረ ብሄራዊ ውህድ ፓርቲ የመቀየሩ ሃሳብ ዋነኛ ምክንያቶች አሁን ያለው የግንባሩ አደረጃጀት አባል ድርጅቶች የጋራ አሰራርን በሚጥሱ ጊዜ የድርጅቱ የውስጥ ጥንካሬ አደጋ ላይ የሚወድቅ መሆኑ፣ የግንባሩ የተጠናከረ ሀገራዊ አንድነት በመፍጠር አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመፍጠር ግቡን በተሟላ ሁኔታ ማሳካት አለመቻሉ፣ አጋር ተብለው የሚጠሩ ድርጅቶችን ከውሳኔ ሰጪነት ያገለለና የሚመሯቸውን ክልሎችና ህዝቦች አቃፊ ባለመሆኑ፣ ማንኛውም የሀገሪቱ ዜጋ በቀጥታ የድርጅቱ አባል ሆኖ መታገል የሚችልበትን እድል የሚሰጥ ያለመሆኑን እና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል አደረጃጀት እንዲኖር ታሳቢ በማድረግ እንጂ ህወሃት በመግለጫዎቹ ባስቀመጣቸው ምክንያቶች እንዳልሆነ መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች እንደሚገነዘቡት እንተማመናለን።
በተጨማሪም ከዚህ አጀንዳ በተያያዘ በቀጣዮቹ ጊዜያት በየደረጃው የሚገኙ የድርጅቱ መዋቅሮች (መድረኮች) የሚወስኗቸውን ውሳኔዎች የድርጅቱ አሰራር በሚፈቅደው ዲሲፒሊን መሰረት ለመላው የድርጅታችን መዋቅርና ለሀገራችን ህዝቦች መረጃዎችን የምንሰጥና ግልፅ እያደረግን የምንሄድ መሆናችንን በዚሁ አጋጣሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን።


Thursday, October 17, 2019

በአፋር ክልል በተለያዩ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎች ተደረጉ

በአፋር ክልል በተለያዩ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎች ተደረጉ

በአፋር ክልል በአፋምቦ ወረዳ በኦብኖ ቀበሌ በሚኖሩ ንፁሃን አርብቶ አደር ሴቶች፣ ህፃናትና አዛውንቶች ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ ነው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሰላማዊ ሰልፍ የወጡት፡፡ በጥቃቱ በርካታ ዜጎች በታጠቁ ኃይሎች ተገለዋል፣ ሴቶች ተደፍረዋል፣ ንብረት ወድሙዋል። እነዚህ የታጠቁ ኃይሎች እነማን እንደሆኑና ከየት እንደመጡ እስካሁን መንግሥት የሰጠዉ መግለጫ የለም። ሆኖም ግን ጥቃቱ በተቀነባበረ ሙልኩ የተፈፀመ መሆኑን ነዋሪዎች ገልፀዋል።
በክልሉ ሰመራና አዋሽ ሰባት ኪሎን ጨምሮ ከሠሞኑ ሰልፍ ባልተካሄደባቸው የተለያዩ ከተሞች ሕዝቡ ዛሬ ጠዋት ወደ አደባባይ መውጣቱ ነው የተገለጸው፡፡
በከተሞቹ እየተካሄደ ያለው ህዝባዊ ሰልፍ ዋና ዓላማው በንጹሃን ዜጎች ላይ በውስጥም ይሁን በውጭ ኃይሎች የሚደርሰውን ጥቃት ማውገዝና እንዲቆም መጠየቅ ነው ተብሏል፡፡
ሰልፈኞቹ መንግስት ጣልቃ በመግባት ዜጎቹን የመጠበቅና በእነርሱ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት የመከላከል ግዴታውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡







Wednesday, October 16, 2019

የጸጥታ መደፍረስ የተስተዋለባቸውን ማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች፣ ጎንደር ከተማና ቅማንት ብሔረሰብ አስተዳድርን የፌዴራል የፀጥታ ኃይል ህጋዊ እርምጃ ወስዶ እንዲያረጋጋ መመሪያ ተላላፈ

የጸጥታ መደፍረስ የተስተዋለባቸውን ማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች፣ ጎንደር ከተማና ቅማንት ብሔረሰብ አስተዳድርን የፌዴራል የፀጥታ ኃይል ህጋዊ እርምጃ ወስዶ እንዲያረጋጋ መመሪያ ተላላፈ

የጸጥታ መደፍረስ የተስተዋለባቸውን ማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች፣ ጎንደር ከተማና ቅማንት ብሔረሰብ አስተዳድር የፌዴራል የፀጥታ ኃይል ህጋዊ እርምጃ ወስዶ ወደ ተሟላ ሰላም እና መረጋጋት እንዲያሸጋግር መመሪያ ተላላፈ።
የአማራ ብሔራዊ ክልል የደኅንነትና የፀጥታ ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ በአካባቢዎቹ ማንነትን ሽፋን በማድረግ ባለፉት አምስት ዓመታት የዘለቀው የጸጥታ መደፍረስ ለሰው ህይዎትና ለንብረት ጥፋት ምክንያት ሆኖ መቀጠሉን አንስቷል።
ችግሩ አካባቢውን ወደ ተሟላ ትርምስ የሚያስገባና ለክልሉ ብሎም ለመላው ሃገሪቱ የጸጥታ ስጋት ወደ መሆን ተሸጋግሯልም ነው ያለው።
በመሆኑም የክልሉ መንግሥት ለፌዴራል መንግሥት ጉዳዩን ጣልቃ ገብቶ እንዲያስተካክል በጠየቀው መሠረት የፌዴራል የፀጥታ ኃይል መከላከያን ጨምሮ ማንኛውም ህጋዊ እርምጃ ወስዶ ቀጠናውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተሟላ ሰላም እና መረጋጋት እንዲያሸጋግር መመሪያ መተላለፉን አስታውቋል።
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦
የአማራ ክልል ደኅንነትና የጸጥታ ካውንስል የጋራ መግለጫና ውሳኔዎች
በማዕከላዊ እና በምዕራብ ጎንደር ዞኖች፣ በጎንደር ከተማ እንዲሁም በቅማንት ብሔረሰብ አስተዳድር ማንነትን ሽፋን በማድረግ ባለፉት አምስት ዓመታት የዘለቀው የጸጥታ መደፍረስ ለሰው ህይዎትና ለንብረት ጥፋት ምክንያት ሆኖ መቀጠሉ የሚታወስ ነው፡፡ የክልሉ መንግስት ህግና ሥርዓትን በተከተለ አኳኋን ለተነሱ የማንነት ጥያቄዎች የቅማንት ብሔረሰብን ጨምሮ ምላሽ መስጠቱ የሚታወስ ነው፡፡ ለተነሱ የማንነት ጥያቄዎችና መልሶች ቅሬታ ያቀረበ ኃይል፣ ቡድንና ማኅበረሰብ ህግና ሥርዓትን በተከተለ መንገድ ሀሳባቸውን፣ ጥያቄያቸውንና ቅሬታቸውን አቅረበው መስተናገድ እየተቻለና ለዚህም በርካታ ዕድሎች ብሎም ጊዜያት ተሰጥተው እያለ በሃይል ፍላጎትን ለማሳካት መሞከር ጸረ ህገ መንግስትና የለዬለት ጸረ ሰላም ተግባር መሆኑ በግልጽ ሊታወቅ ይገባል፡፡
የቅማንት የራስ አሥተዳድር ኮሚቴ የተከተለው አቅጣጫም ከላይ የተገለጹ ተግባራትን በመፈጸም ፍላጎትን በኃይል በብሔረሰቡና በክልሉ መንግስት ላይ የመጫን ኢ ህገ መንግስታዊ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ይህንን ለመቀልበስ የሚወሰድ አጸፋዊ እርምጃም በአንጻሩ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል፡፡ ከመስከረም 15/2012 ዓ.ም ጀምሮ የተከሰተው ግጭትና እያደረሰ ያለው ከፍተኛ ጉዳትም የዚህ መገለጫ ነው፡፡ ለአካባቢው ጸጥታ መደፍረስ ምክንያት ሆኗል፤ ለሌሎች የጥፋት ሃይሎችም ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር እያደረገ ነው፡፡ በዚህም የተለያዬ ኢ መደበኛ አደረጃጀትን ይዘው የሚንቀሳቀሱና በጸረ ሰላም ተግባር ላይ የተሰማሩ ቡድኖችና ግለሰቦችም ትልቅ መሳሪያ አድርገው እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ በዚህም በሰው ህይዎትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ይገኛል፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በክልልና በፌዴራል መንግስት በትዕግስትና በአርቆ አስተዋይነት ችግሩን በሰላማዊ አግባብ ለመፍታት በርካታ ጥረቶች ቢደረጉም ወደ ውጤት ሊቀየር አልቻለም፡፡ ይባስ ብሎም አካባቢውን ወደ ተሟላ ትርምስ የሚያስገባና ለክልሉ ብሎም ለመላው ሃገሪቱ የጸጥታ ስጋት ወደ መሆን ተሸጋግሯል፡፡ የሰው ህይወትና ንብረት በየቀኑ ይጠፋል፡፡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በከፍተኛ ደረጃ ተዳክመዋል፡፡ ከጎንደር-መተማ ያለው አከባቢ የንግድ መስመር ከመሆኑ ጋር ተያይዞም በገቢና ወጪ ንግድ ላይም ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ በመሆኑም የክልሉ መንግሥት ለፌዴራል መንግሥት ጉዳዩን ጣልቃ ገብቶ እንዲያስተካክል በጠየቀው መሠረት የፌዴራል የፀጥታ ኃይል መከላከያን ጨምሮ ማንኛውም ህጋዊ እርምጃ ወስዶ ቀጠናውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተሟላ ሰላም እና መረጋጋት እንዲያሸጋግር መመሪያ ተላልፏል፡፡
የተላለፈውን መመሪያ በመከተል የክልሉ የፀጥታና ደኅንነት ካውንስል በማዕከላዊ፣ በምዕራብ ጎንደር፣ በቅማንት ብሔረሰብ አስተዳድር እና በጎንደር ከተማ ቀጥለው የቀረቡ ክልከላዎችና ውሳኔዎች ተግባራዊ እንዲደረጉ መመሪያ ሠጥቷል፡፡
1.ማንኛውም የኃይል እንቅስቃሴን የኃይል እርምጃ በመውሰድ የሰው ህይወትና ንብረትን ከአደጋ ማዳን፣ በድርጊቱ ላይ የተሳተፉትን በኃይል መቆጣጠር፣ ለህግ ማቅረብ፣ ተመጣጣኝ የኃይል እርምጃን በመውሰድ የኃይል ተግባርን ፍፁም እንዳይቀጥል ማድረግ፣
2.አሁንም የሰላም አማራጮችን ለማስፋትና በአከባቢው ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ሲባል በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ግጭት የገቡ ቡድኖች እና ግለሰቦች በአስቸኳይ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ በመመለስ ያሏቸውን ልዩነቶች እንዲፈቱ ጥሪ ተላልፏል፡፡ ከዚያ ውጪ ምንም ዓይነት የኃይል እርምጃ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡
3.ማንኛውም ግለሰብ ወይም ቡድን በቀጠናው ላይ ለሚደረገው የፀጥታ ኃይል ስምሪት የመተባበር፣ ወንጀለኛን አሳልፎ የመስጠትና የአከባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ የሚደረገውን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ድጋፍ የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡ ይህንን የሚያደናቅፍ ማንኛውም ተግባር በህጋዊ እርምጃ የሚስተካከል ይሆናል፡፡
4.በግልፅ በታወቁ የፀጥታ ኃይሎች ከተያዙት ትጥቅና መሳሪያ ውጪ በተጠቀሱት የክልሉ ዞኖች ላልተወሰነ ጊዜ ትጥቅ ይዞ መንቀሳቀስ የተከለከለና የሚወረስ ይሆናል፡፡
5.የቅማንት ብሔረሰብ አስተዳድር ከዚህ ቀደም በተወሰነው ህጋዊ ውሳኔ መሠረት በአፋጣኝ በሕዝብ ይሁንታ የሚደራጅ የራስ አስተዳድርን በማቋቋም ሁሉም አገልግሎት እንዲጀምር ማድረግ፡፡ ይህንን የሚያደናቅፍ የኃይል እርምጃ ፍፁም ተቀባይነት አይኖረውም፡፡
6.በተለያየ ምክንያትና ሰበብ ተደናግሮም ይሁን በንቃት በኃይል ፍላጎትን ለማሳካት በተደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፎ የነበረውን ኃይል፣ ቡድንና ግለሰብ እስከ ጥቅምት 20/2012 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመለስ የክልሉ መንግሥት በድጋሜ ይቅርታ አድርጎለታል፡፡ በሰው ግድያ ቀጥተኛ ተሳትፎ የነበራቸው ግለሰቦች ጉዳያቸው በህግ አግባብ የሚታይ መሆኑ እንደተጠበቀ ይሆናል፡፡
7.በየዞኑ፣ በየወረዳውና ቀበሌ ውስጥ፣ አቅራቢያና አከባቢ ለሚፈጠሩ ወንጀሎች ፀረ-ሰላም ድርጊቶችና እንቅስቃሴዎች በየደረጃው ያለው አመራር፣ ነዋሪና ዜጋ የመቆጣጠር፣ የማሳወቅ፣ እርምጃ እንዲወስድ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ተጠያቂነትን ከማስከተልም በተጨማሪ በአከባቢው የሚገኘው ትጥቅ ሙሉ በሙሉ ተራግፎ ለመንግሥት ገቢ ይሆናል፡፡
8.በኢ- መደበኛ አደረጃጀትና ባልተሠጠ ኃላፊነት ህግን ለማስከበር በሚል ሰበብ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ የተከለከለ ነው፤ ተጠያቂነትም ያስከትላል፡፡
9. ከጎንደር-መተማ ፣ ከጎንደር-ሁመራ፣ ከጎንደር-ባሕር ዳር፣ ከጎንደር- ደባርቅ የሚወስዱ መንገዶች እንዲሁም በጎንደር ከተማና ዙሪያው ብሎም ሁሉም መጋቢና ዋና ዋና መንገዶች በማንኛውም ጊዜ ነፃ ይሆናሉ፡፡ የሕዝብ እንቅስቃሴም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ነፃ ይሆናል፡፡ ይህንን ለማደናቀፍ የሚደረግ እንቅስቃሴ ላይ ህጋዊ እርምጃ የሚወሰድ ይሆናል፡፡
10.የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ ክልል የፀጥታ ኃይል፣ በየደረጃው ያለው የክልሉ መስተዳድር፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት በቅንጅትና በጥምረት በመሰማራት በአከባቢው ላይ የተሟላ ሰላምና መረጋጋትን እንዲፈጠር ያደርጋሉ፡፡
11.በመጨረሻም ሁሉም የሰላም ኃይሎች ማለትም የሃይማኖተ አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ብሔርን እና ማንነትን ሳይለይ በአከባቢያችን የተሟላ ሰላም እንዲረጋገጥ ለፀጥታ ኃይሉ የተሟላ ድጋፍ ታደርጉ ዘንድ ጥሪያችን እናስተላልፋለን፡፡
የአማራ ብሔራዊ ክልል የደኅንነትና የፀጥታ ካውንስል፡፡
ጥቅምት 5፣ 2012 





የህወሓት መግለጫና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ምላሽ

 የህወሓት መግለጫና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ምላሽ

የኢህአዴግ ጽሕፈት ቤትም ምላሽ ሰጥቷል
የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ለሰባት ቀናት ሲያካሄድ የነበረውን ስብሰባ በማጠናቀቅ መግለጫ አውጥቷል:: ህወሓት በመግለጫው “እሳትና ጭድ የሆኑ ፓርቲዎች ሊዋሃዱ አይችሉም ከተዋሃዱም ኢህአዴግ ከማፍረስ ባሻገር ሃገርን ያፈርሳል” ብልዋል::
የኢህአዴግ ፅሕፈት ቤት በበኩሉ “ውህደቱ ሃገራዊ አንድነት የሚፈጥር መሆኑን ያካሄድኩት ጥናት አሳይቷል” ብሏል::
በሌላ በኩል የጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት የፕሬስ ኃላፊ ወይም የፕሬስ ሴክሬታሪ ንጉሡ ጥላሁን በሰጡት ምላሽ፤ “በህወሓት የወጣው መግለጫ ለውጡ ከመጣላት ሳይሆን ከመጣበት ሕዝብን የማይወክል አካል የወጣ ነው” ብለዋል፡፡
ለዚህም ምክንያቱም “መግለጫውን ያወጣው ቡድን በለውጡ ምክንያት የተቋረጠበት ጥቅምና መኖሩንና የነበረው ግፍ እንዲመለስ መመኘቱ ነው” ብለዋል፡፡ ህወሓት የኢህ አዴግን የውህደት እንቅስቃሴ አስመልክቶ በመግለጫው ያሰፈረውም ለዓመታት ሲያንፀባርቀው ከነበረው አቋም የተለየ እንደሆነ አቶ ንጉሡ ተናግረዋል፡፡ 

ተጨማሪ መረጃዎች እንደደረሰን ሰፋ ያለ ዘገባ እናቀርባለን





ለማ መገርሳ ለዶ/ር አብይ ሽልማት አበረከተ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሽልማት የኢትዮጵያ ተሰሚነት ከፍ ማለቱን ያሳያል- አቶ ለማ መገርሳ
የመከላከያ ሚኒስትርና የኦሮሞ ዴሞክራክ ፓርቲ ም/ ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳ ፓርቲያቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የኖቤል የሰላም ተሸላሚ መሆናቸው ተከትሎ ስጦታ ባበረከተላቸው ወቅት እንደገለጹት፣ ሽልማቱ የኢትዮጵያ ተሰሚነት አንድ ደረጃ ከፍ የማለቱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያገኙት ሽልማት የሁሉም የአገሪቱ ህዝቦች ሽልማት ነው ብለዋል አቶ ለማ፡፡
አቶ ለማ መገርሳ ሌሎች ተመሳሳይ ሽልማቶችን ለማሸነፍ ጠንክረን መስራት አለብን ብለዋል፡፡
የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ማዕከላዊ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው፣ ሽልማቱ ሰላም ወዳድነታችን የዓለም አቀፍ እውቅና የማግኘቱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡






ሌሎችን መረጃ ለማግኘት የሚከተሉትን ፅሑፍ ይጫኑ 

Tuesday, October 15, 2019

ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ዛሬ በልደታ ኮንደሚኒየም አስገራሚ ነገር በማድረግ ነዋሪዉን ሳርፕራይዝ አደረጉ ለማየት ሊንኩን ይጫኑ

ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ዛሬ በልደታ ኮንደሚኒየም አስገራሚ ነገር በማድረግ ነዋሪዉን ሳርፕራይዝ አደረጉ ለማየት ሊንኩን ይጫኑ http://bit.ly/2OQqVze 

ህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን እስከ ሞት የሚያስቀጣ የህግ ማዕቀፍ እየተጠናቀቀ ነው


ህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን እስከ ሞት የሚያስቀጣ የህግ ማዕቀፍ እየተጠናቀቀ ነው
*****************************************************
ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን፣ የድንበር ማሻገርና በሰው መነገድ ወንጀሎችን መቆጣጠር ያስችላል የተባለውና እስከሞት የሚያስቀጣ አንቀጾችን ያካተተ ጠንከር ያለ የህግ ማዕቀፍ እየተጠናቀቀ መሆኑን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ፡፡
በፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱሉ እንደተናገሩት በርካታ አምራች ወጣቶች በደላሎችና በህገ ወጥ ድንበር አሻጋሪዎች ለእንግልት፣ ለስቃይ እንዲሁም ለሞት እየተዳረጉ በመሆኑ ወንጀሉን ለመቆጣጠር የሚያስችል ጠንካር ያለ የህግ ማዕቀፍ አስፈልጓል፡፡
በወንጀል ድርጊቱ በርካታ ወጣቶች የአካላዊ፣ ስነ-ልቦናዊና አልፎም የህይወት መጥፋት እየደረሰባቸው ይገኛል፡፡
በሀገራቸው መስራትና ማምረት የሚችሉ በርካታ ወጣቶች በደላሎችና ህገ ወጥ ድንበር አሻጋሪዎች ተጠቂ በመሆናቸው ለጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑም አክለዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ተገቢ ቅጣት እንዲያገኙ የሚያደርግ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ረቂቅ አዋጁ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ለህግና ፍትህ ዴሞክራሲያዊ ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም ለሴቶች፣ወጣቶችናማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ ቀርቧል ተብሏል፡፡
ጉዳዩ አስከፊና አሳሳቢ መሆኑን ተከትሎ ከሚቀርቡትና ቶሎ ከሚጸድቁት የህግ ማዕቀፎች ውስጥ ቅድሚያ እንዲያገኝ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ወንጀሉ በሃገር ውስጥና በውጭ ሃይሎች በቅንጅት የሚሰራ በመሆኑ ችግሩን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ድንበር አካባቢ ካሉ ጎረቤት አገራት ጋር በቅንጅትና በትብብር ለመስራት ስምምነት ላይ እንደተደረሰ አቶ ዝናቡ ገልጸዋል፡፡
ችግሩንም በዘላቂነትለመፍታት የህግ ማዕቀፎች ማዘጋጀቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ህብረተሰቡ ላይ ለውጥ ማምጣጥት የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ላይ እና የስራ አድል ፈጠራ ላይ በስፋት መስራት እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡
ወጣቱ በሃገሩ ሰርቶ የሚለወጥበት፣ሃብት ንብረት የሚያፈራበት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
በዚህ ወንጀል ድርጊት የሚሳተፉ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ከጸጥታ ሃይሉ ጎን ለጎን የህብረትሰቡ ትብብር፣ የወንጀሉ ተጎጅ አካላት ተባባሪ መሆን ወሳኝ ነውም ነው የተባለው፡፡


አዳዲስ መረጃዎችንና ዜናዎችን ለማግኘት የዩቱብ ቻናላችንን ሳብስክራይብ ያደርጉ። የተለያዩ መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን ርዕሶችን ይጫኑ።

Monday, October 14, 2019

አንድነት ፓርክ ሙሉ መረጃ

ፓርኩን ለማየት ይህን ይጫኑ የቤተመንግሥቱ አንድነት ፓርክ
በታላቁ ቤተመንግሥት የተገነባዉ ዉብና ማራኪ የሆነዉ አንድነት ፓርክ ሐሙስ መስከረም 29/2012 ተመርቆ ተከፈተ። 
በፓርኩ ዉስጥ የሀገሪቱን ገፅታ ሊያሳዩ የሚችሉ ብርካታ ሥራዎች ተሠርቶ ልጉብኝት ክፍት ሆነዋል።
የቀድሞ መሪዎች ቢሮዎችና መኖሪያዎቻቸዉ ለህዝብ ጉብኝት ክፍት ሆነዋል።
የነገሥታት ምስል በሚያምር ሁኔታ ተቀርፆ ይታያል።

ሙሉ መረጃን ለማየት ይህን ፅሑፍ ይጫኑ ስለ አንድነት ፓርክ ሙሉ መረጃ

ከኢህአዴግ ምክር ቤት ፅ/ቤት የተሰጠ መግለጫ

ከኢህአዴግ ምክር ቤት ፅ/ቤት የተሰጠ መግለጫ ኢህአዴግን ከግንባርነት ወደ አንድ ህብረ ብሄራዊ ውህድ ፓርቲ የማሸጋገር ጉዳይ በ1996 ዓ.ም ከተካሄደው 5ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ጀምሮ በተከታታይ በተካሄዱት የድርጅቱ ጉባ...